- “እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ወስዶ ያበጃትም ይጠብቃትም ዘንድ በኤዶም ገነት አኖረው” (ዘፍ.፪፥፲፭)
የጮቢ መካነ ሕይወት በዓታ ለማርያም የአንድነት ገዳም
“እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ወስዶ ያበጃትም ይጠብቃትም ዘንድ በኤዶም ገነት አኖረው” (ዘፍ.፪፥፲፭) ተብሎ እንደተጻፈ ሰው ቦታን ይቀድሳል። በአንጻሩም ሰዎች በቦታ ይቀደሳሉ። ይልቁንም የቅዱሳን የጸሎት በዓታቸው የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ያለበት፣ የቅዱሳኑ አጽማቸው የረገፈበት ስለሆነ በረከተ ሥጋን በረከተ ነፍስን ያድለናል።
መካነ ሕይወት ጮቢ በዓታ ለማርያም አንድነት ገዳም የሚገኘው በምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት በዱግዳ ቦራ ወረዳ ሀርቦ አቡኖ ቁሙሮ ቀበሌ ገበሬ ማኅበር ነው፡፡ በመካከለኛው ምሥራቅ አቅጣጫ ከአዲስ አበባ እስከ ኬላ ከተማ ድረስ ፻፲፫ ኪሎ ሜትር ርቀት ያለው ሲሆን፤ ከኬላ ከተማ ገዳሙ ድረስ ደግሞ ያለው ጥርጊያ መንገድ ፲፭ ኪሎ ሜትር ይሆናል፡፡ "ጮቢ" ማለት በኦሮሚኛ በረከት ማለት ሲሆን፤ የገዳሙ አካባቢ ደግሞ አቡኖ በመባል የሚጠራ ነው፡፡ ይህንንም ስያሜ ያገኘበት ምክንያት በጥንት ጊዜ ቦታው ላይ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ እና አቡነ ተክለ ሃይማኖት ያረፉበት በመሆኑ እንደሆነ የገዳሙ አባቶች ያስረዳሉ፡፡
የገዳሙ አመሠራረት መካነ ሕይወት ጮቢ በዓታ ለማርያም አንድነት ገዳም የተመሠረተው በእግዚአብሔር መልካም ፈቃድ በ፲፱፻፺፫ ዓ.ም. ነው፡፡ መሥራቹም የምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል የሆኑት ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ሣልሳዊ ናቸው፡፡ አሁን እየተጠራበት ያለውን ስያሜ ያገኘው ግን ሰኔ ፬/፲፱፻፺፰ ዓ.ም ነው፡፡
ዛሬ የሚታየው ልማት ከመምጣቱና ከመስፋፋቱ በፊት ቦታው ጠፍ እና ምንም የሌለበት የእርሻ መሬት ነበር፡፡ በወቅቱ ፭ እናቶች እና ሁለት አባቶች በጊዜው ቡታጅራ ማረሚያ ቤት ለእስር ከተዳረጉ እና የእስር ጊዜቸውን ጨርሰው በነጻ ከተለቀቁ በኋላ ወደ ሥፍራው በማቅናት አከባቢውን ሲቃኙ አስቀድሞ ቦታው ለእግዚአብሔር ማደሪያ የተመረጠ መሆኑን በመረዳት በእኒሁ አባቶች እና እናቶች ተነሣሽነት በብፁእ አቡነ ጎርጎርዮስ ሣልስ የምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ መልካም ፈቃድ የመሠረት ድንጋይ ተቀመጠ፡፡ ለሐሳቡ እውን መሆን አቶ አማረ ዱቤ የሚባሉ የአከባቢው ነዋሪ እና የሀገር ሽማግሌ የሆኑ የአባቶችን ሐሳብ በመቀበል የራሳቸውን የእርሻ መሬት ለቤተ ክርስቲያኑ በመስጠት አሁን ያለችው የቤተ ክርስቲያን መቃኞ ሰኔ ፲፭/ ፲፱፻፺፭ ዓ.ም. ተጀምሮ በ፮ ወር ታንጾ ታኅሣሥ ፫ ቀን ፲፱፻፺፮ ዓ.ም. ተጠናቆ ቅዳሴ ቤቷ ተከበረ፡፡
፫. የገዳሙ ሥርዓተ አበው
፫.፩. አንድነት ገዳሙ የአንድነት ገዳም በመሆኑ ጠንካራ የአንድነት ሥርዓት አለው፡፡ በዚህ ገዳም ቁሪት (የግል ሀብት) አጥብቆ የተከለከለ ነው፡፡ በገዳሙ በምናኔ የሚኖርም ሆነ በእንግድነት የመጣ ማንኛውም ሰው የገዳሙን የአንድነት ስርዓት የማክበር ግደታ አለበት። ምዕመናን ወደ ገዳሙ ሲመጡ በመናንያን ላይ መሰናክል እንዳይሆኑ ክትትል ይደረግባቸዋል፡፡ የጠበልተኞች ማረፊያ ለብቻ የተዘጋጀ ሲሆን ወደ እናቶች ገዳም መግባት በጥብቅ ይከለከላል፡፡ ማንኛውም የማኅበር አባል ለግል ጉዳይ በልዩ ልዩ ምክንያትና ችግሮች ወደ ሌላ ቦታ ደርሶ ለመመለስ ያሰበ እንደሆነ አስቀድሞ መምህሩን ወይም መጋቢውን ወይም ሊቀ አርድዕቱን ማስፈቀድ ይኖርበታል፡፡ መናንያን ፫ ዓመት እና ከዚያ በላይ ገዳሙን ካገለገሉ በየዓመቱ በገዳሙ ወጪ ተሸፍኖላቸው ታሪካዊ ገዳማት በመጎብኘት ከበረከት እንዲሳተፉ ይደረጋል፡፡ ለእናቶችም ወርኃዊ የንጽሕና መጠበቂያ በወቅቱ ይሟላላቸዋል፡፡ ከአቅም በላይ ከሆነ ግን ወደ ገዳሙ አስተዳደር ቀርቦ ውሳኔ ይሰጥበታል፡፡
ወደ ገዳሙ ለመግባት የሚፈልጉ መናንያን በገዳሙ ሕግና ሥርዓት መሠረት የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አማኝ ሆኖ በሃይማኖቱ ሕጸጽ የሌለበት፣ በገዳሙ ደንብ ለመተዳደር ፈቃደኛ የሆነ፣ ከመጣበት አካባቢ ማንነቱን የሚያስረዳ በቂ ማስረጃ ያለው መሆን አለበት፡፡ ከሌላ ገዳም የሚመጣ መናኒ የማኅበሩ አባል ለመሆን ሲያመለክት ከመጣበት ገዳም በቂ ማስረጃ ማቅረብ ይኖርበታል፡፡ አንድ የማኅበር አባል የገዳም ኗሪነቱን የሚገልጽ መታወቂያ ወረቀት ሚያገኘው በገዳሙ ውስጥ አባል ሆኖ ቢያንስ አንድ ዓመት የቆየ እንደሆነ ነው፡፡ በአሁ ጊዜ በገዳሙ ተገኝተን በተመለከትነው መረጃ በገዳሙ ውስጥ የሚገኙ መናንያን አባቶች ፲፱ እናቶች ፲፮ በአጠቃላይ ፴፭ ናቸው፡፡
በገዳሙ የጸሎት ሥርዐት በቀን ሰባት ጊዜ የሚጸለይ ሲሆን፤ እነዚህም በመዓልት በ፫፣ በ፮፣ በ፱፣ በ፲፩፣ በሌሊት በ፫፣ በ፮፣ በ፱ ናቸው፡፡ ዘወትር በጠዋት ኪዳን ይደረሳል፡፡ መነኰሳይያት የማታ ጉባኤ እና ትምህርት አላቸው፡፡
በገዳሙ መናንያን ከሰኞ እስከ ዓርብ በሁለት ቀን አንድ ጊዜ በ፱ ሰዓት፣ ቅዳሜ እና እሑድ በ፫ ሰዓት አንድ ዳቤ የሚሰጣቸው ሲሆን፣ በሥራ ላይ ለሚሰማሩት ግን በየቀኑ ምሳ ላይ እንጀራ ይሰጣቸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ለአብነት ተማሪዎች በቀን ሁለት ጊዜ እንጀራ ይሰጣቸዋል፡፡ መናንያኑ የሚለብሱት ሁሉም አንድ አይነት የሆነ እና በገዳሙ መናንያን ከቅጠላቅጠል በሚዘጋጅ ቀለም የሚነከር ቀይ ቡኒ ቀለም ያለው አቡጀዲ ሲሆን፤ አሰፋፉም የገዳማውያንን ሥርዓት የተከተለ ነው፡፡
በአጋጣሚ በመናንያን መካከል አለመግባባት ቢፈጠር በራሳቸው እንዲፈቱ ይደረጋል፡፡ ነገር ግን ከገዳሙ ሥርዐት የወጣ መናኒን እንደ ጥፋቱ መጠን የተለያዩ ቅጣቶች ይሰጡታል፡፡ እነዚህም የጉልበት ሥራ (እንጨት ለቀማ፣ ፅዳት እና የመሳሰሉት)፣ ስግደት፣ በእግር ብረት መታሰር ሲሆኑ፣ ከነዚህም ቅጣቶች ጎን ለጎን ተግሣፅ እና ምክርን ያካትታል፡፡
በገዳሙ ተሠርተው አገልግሎት እየሰጡ ያሉ የልማት ውጤቶች
