መካነ ሕይወት ጮቢ በዓታ ለማርያም አንድነት ገዳም
የገዳሙ መገኛ ቦታ፡- መካነ ሕይወት ጮቢ በዓታ ለማርያም አንድነት ገዳም የሚገኘው በምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት በዱግዳ ቦራ ወረዳ ሀርቦ አቡኖ ቁሙሮ ቀበሌ ገበሬ ማኅበር ነው፡፡ በመካከለኛው ምሥራቅ አቅጣጫ ከአዲስ አበባ እስከ ኬላ ከተማ ድረስ ፻፲፫ ኪሎ ሜትር ርቀት ያለው ሲሆን፤ ከኬላ ከተማ ገዳሙ ድረስ ደግሞ ያለው ጥርጊያ መንገድ ፲፭ ኪሎ ሜትር ይሆናል፡፡ "ጮቢ" ማለት በኦሮሚኛ በረከት ማለት ሲሆን፤ የገዳሙ አካባቢ ደግሞ አቡኖ በመባል የሚጠራ ነው፡፡ ይህንንም ስያሜ ያገኘበት ምክንያት በጥንት ጊዜ ቦታው ላይ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ እና አቡነ ተክለ ሃይማኖት ያረፉበት በመሆኑ እንደሆነ የገዳሙ አባቶች ያስረዳሉ፡፡ ከገዳሙ በስተ ምዕራብ አቅጣጫ በተራራ የተከበበ እና የተለያዩ ዕፅዋቶች የሚገኙበት ሲሆን፣ ሰፋፊ የእርሻ መሬት ያለበት ሜዳ እና ገደላማ ነው፡፡ በገዳሙ አካባቢ የሚኖሩ ምዕመናን የሶዶ ጉራጌ ሲሆኑ፤ መለያ ስማቸው ግን ሶዶ ክስታኔ በመባል ይታወቃሉ፡፡ ይህንንም ስያሜ ያገኙት በጣሊያን ጊዜ በመስቃን ጦርነት ከአርሲ ሙስሊሞች ጋር ተዋግተው ብዙዎች ሰማዕትነት ተቀብለዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በግራኝ አሕመድ ወረራ ጊዜም ሃይማኖታቸውን ሳይቀይሩ ፀንተው የቆዩ ክርስቲያኖች በመሆናቸው ነው፡፡
የገዳሙ አመሠራረት
መካነ ሕይወት ጮቢ በዓታ ለማርያም አንድነት ገዳም የተመሠረተው በእግዚአብሔር መልካም ፈቃድ በ፲፱፻፺፫ ዓ.ም. ነው፡፡ መሥራቹም የምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል የሆኑት ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ሣልሳዊ ናቸው፡፡ አሁን እየተጠራበት ያለውን ስያሜ ያገኘው ግን ሰኔ ፬/፲፱፻፺፰ ዓ.ም ነው፡፡ ዛሬ የሚታየው ልማት ከመምጣቱና ከመስፋፋቱ በፊት ቦታው ጠፍ እና ምንም የሌለበት የእርሻ መሬት ነበር፡፡ በወቅቱ ፭ እናቶች እና ሁለት አባቶች በጊዜው ቡታጅራ ማረሚያ ቤት ለእስር ከተዳረጉ እና የእስር ጊዜቸውን ጨርሰው በነጻ ከተለቀቁ በኋላ ወደ ሥፍራው በማቅናት አከባቢውን ሲቃኙ አስቀድሞ ቦታው ለእግዚአብሔር ማደሪያ የተመረጠ መሆኑን በመረዳት በእኒሁ አባቶች እና እናቶች ተነሣሽነት በብፁእ አቡነ ጎርጎርዮስ ሣልስ የምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ መልካም ፈቃድ የመሠረት ድንጋይ ተቀመጠ፡፡ ለሐሳቡ እውን መሆን አቶ አማረ ዱቤ የሚባሉ የአከባቢው ነዋሪ እና የሀገር ሽማግሌ የሆኑ የአባቶችን ሐሳብ በመቀበል የራሳቸውን የእርሻ መሬት ለቤተ ክርስቲያኑ በመስጠት አሁን ያለችው የቤተ ክርስቲያን መቃኞ ሰኔ ፲፭/ ፲፱፻፺፭ ዓ.ም. ተጀምሮ በ፮ ወር ታንጾ ታኅሣሥ ፫ ቀን ፲፱፻፺፮ ዓ.ም. ተጠናቆ ቅዳሴ ቤቷ ተከበረ፡፡
በተለይ አሁን ያሉት የገዳሙ አበ ምኔት መ/ር አባ ተ/ሥላሴ በሳል የአመራር ሰጪነት በአባ ገ/እግዚአብሔር እና አባ ኃ/ገብርኤል አጋዥነት የመጀመሪያ ተግባር የነበረው የገዳሙን ይዞታ ማስፋፋት ስለነበር እስከ ፲፱፻፺፰ ዓ.ም. ይህን ዐቢይ ተግባር በሰፊው ቀጥለውበታል፡፡ የገዳሙ ይዞታ ፹፩.፸፱ (ሰማንያ አንድ ነጥብ ሰባ ዘጠኝ) ሄክታር ሲሆን የይዞታ ማረጋገጫ ደብተርም ተሰጥቶታል፡፡ ወደ ፊትም ይዞታን የማስፋቱ ሥራ የሚቀጥል ይሆናል፡፡ የእኒህ አባቶች ምኞት እና ራእይ ለትውልዱ አርዓያ የሚሆንና ለችግረኞች መጠጊያ ሊሆን የሚችል ገዳም መመሥረት በመሆኑ ከሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ጎን ለጎን ተግባር ቤት እና የእናቶች ማደሪያ ሠሩ፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ገዳሙ፣ የገዳሙ መናንያንና ልማት የማይነጣጠሉ የአንድ ሳንቲም ገጽታ ሆኑ፡፡
ግንባታቸው ያልተጠናቀቁ ሕንጻዎች
ገዳሙ ብዙ የልማት ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል። ይኽም ከላይ ያየናቸው የተለያዩ ግንባታዎች ዋናዎቹ ሲሆኑ ወደፊት የሚጠናቀቁ ግንባታዎች የሚከተሉት ናቸው፡፡
1. የእናቶች በዓት
ገዳሙ የአንድነት ገዳም ቢሆንም የእናቶች እና የአባቶች በዓት መለያየት እንደሚገባ የገዳሙ
መተዳደሪያ ደንብ የሚያስቀምጥ በመሆኑ 18 ክፍላትን የያዘ ሙሉ መገልገያ የሚሟላለት ሕንጻ በመገንባት ላይ ይገኛል።
2. የስብከተ ወንጌል አደራሽ
ለገዳሙ ከሚያስፈልጉት መሠረተ ልማቶች መካከል የስብከተ ወንጌል አዳራሽ አንዱ ነው፡፡ የስብከተ ወንጌል አዳራሽ ዘርፈ ብዙ አገልግሎት ይሰጣል። ለስብከተ ወንጌል አገልግሎት ለሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች መማሪያ ለመንፈሳዊ ጉባኤያት ለእንግዶች መቀበያ እና ማረፊያ ያገለግላል፡፡ ገዳሙም ችግሩን ለመፍታት በማሰብ በአንድ ጊዜ 1000 (አንድ ሺህ) ምእመናንን ማስተናገድ የሚችል አዳራሽ እያስገነባ ይገኛል፡፡
3. ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን
አሁን ያለው ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ገዳሙ ሲመሠረት የተገነባ ሲሆን ከዕድሜ መጨመር እና
የአካባቢው ማኅበረሰብ እየበዛ መሄድ በተፈለገው መጠን ምእመናኑን ማስተናገድ አልተቻለም።
የገዳሙ አስተዳደር አዲስ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን መገንባት አስፈላጊ መሆኑን ካመነበት በኋላ 19 ሚሊየን የሚገመት አዲስ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን መገንባት ተጀምሯል።
የገዳሙ ቋሚ እና ተንቀሳቃሽ ንብረቶች
ገዳሙ ከመናንያኑ ጀምሮ በርካታ ቋሚ እና ተንቀሳቃሽ ንብረቶች ያሉት ሲሆን ዋና ዋናዎቹን ለመጥቀስ
-የይዞታ ማረጋገጫ ያለው 81.79 (ሰማንያ አንድ ነጥብ ሰባ ዘጠኝ) ሄክታር የእርሻ መሬት
-በናፍታ የሚሠራ ሁለት የእህል ወፍጮ
-ሰዎችን እቃንና ምርትን ከቦታ ቦታ የሚያመላልስ ትራክተር
-የብሎኬት ማምረቻ ማሽን
-የሲሚንቶ ማቡኪያ ሚክሰር
-አርማታ ማዋሐጃ ቫይብሬተር
-ከሙአለ ሕጻናት እስከ 4ኛ ክፍል አገልግሎት እየሰጠ ያለ ት/ቤት
-28 የእርሻ በሬዎች
-52 የሐበሻ እና የፈረንጅ ላሞች
-7 አህዮች
-ተገንብተው የተጠናቀቁ እና በመገንባት ላይ ያሉ ሕንጻዎች ዋና ዋናዎቹ ናቸው።
ወደፊት ሊሠሩ የታሰቡ ግንባታዎች
-እያንዳንዱ 24 ክፍሎች ያሉት ባለ አንድ ፎቅ (G+1) የተለያዩ 3 ሕንጻዎች የካህናት ቤት
-ዕቃ ቤት
-ምርፋቅ (የመመገቢያ አዳራቀሽ)
-የወንድ ተግባር ቤት
-የእደ ጥበባት ማእከል (የእንጨት ሥራ የብረታ ብረት ሥራ የሽመና ሥራ)
-የአብነት ትምህርት ቤት ግንባታ
-የከርሠ ምድር ውኃ ቁፋሮ
-የባዮ ጋዝ ቴክኖሎጂ ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡
ገዳሙ ለአከባቢው ማኅበረሰብ እየሰጠ ያለው አገልግሎት
በማንኛውም ደዌ ተይዘው ወደ ገዳሙ ለሚመጡ ምእመናን የጠበል አገልግሎት የሚደረግባቸው ሲሆን ጠበልተኞች የማረፊያ ቦታ ይመቻችላቸዋል በቆይታቸውም መቁነንት ከመናንያን ጋር
ይጣሰቸዋል።
ለአከባቢው ማኅበረሰብ በተለይ በገዳሙ ዙሪያ ለሚኖሩ ምእመናን ማንኛውም ችግር
ሲገጥማቸው ገዳሙ ይደርስላቸዋል፡፡ ለአብነት ያህልም ዘር ሲያጥራቸው ዘር ይሰጣል ከገዳሙ የእርሻ መሬት በየዓመቱ በቂ ምርት የሚሰበሰብ በመሆኑ ከአካባቢው ማኅበረሰብ ባሻገር ለተለያዩ ገዳማትም የቀለብ እገዛ ይደረጋል። በገበያ ቀን ከገዳሙ እስከ ዋናው መንገድ 10 ኪ.ሜ. በእቃ ማጓጓዣ ትራክተር የትራንስፖርት አገልግሎት ይሰጣል በበጋ ወቅት የውኃ እጥረት ሲኖር የመጠጥ ውሃ ያከፋፍላል የወፍጮ አገልግሎት በቅናሽ ዋጋ አቅም ለሌላቸው ደግሞ በነጻ ይፈጫል በኬላ ከተማ ከሙአለ ሕፃናት እስከ 4ኛ ክፍል በከፈተው ት/ቤት በአከባቢው ካሉ የግል ት/ቤቶች በተሻለና ዝቅተኛ ክፍያ ማለትም በአንድ ተማሪ 150 ብር በማስከፈል ያግዛል እጓለ ማውታ (የሙት ልጅ የሆኑ) ሕጻናትን ያሳድጋል።
አካባቢው የገጠር ቀበሌ በመሆኑና ጥርጊያ መንገድ ባለመኖሩ አርሶ አደሩ ምርቱን ወደ ገበያ
ለመውሰድ ሰው ሲታመምበት ወደ ሕክምና ለማድረስ ከፍተኛ ችግር ነበር። ገዳሙም ይህን በመረዳት በራሱ ወጪ 10 ኪ.ሜ. መንገድ በማስጠረግ እና ከዋናው መንገድ ጋር በማገናኘት የተጠቀሱ ችግሮችን መፍታት ችሏል።
መፍትሔ ሊሆኑ የሚችሉ
ለመናንያን ፍልሰት መፍትሔ ሊሆን የሚችለው በዋናነት አጽንኦ በዓት ሲሆን ይህም የሚሆነው አግዚአብሔር ሲፈቅድ እና ሲያጸና መሆኑ በእርግጥ ይታወቃል። ይሁን እንጂ እንደ ሰው ሰውኛ መናንያን በበዓታቸው እንዲጸኑ የተለያዩ ሥልጠናዎች መሥጠትም አንድ መፍትሔ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ የምንኵስና ሕይወት ያሉት ፈተናዎች እና የሚየሰጠው ጸጋ አጽንኦ በዓት እና ሌሎች ተዛማች ሥልጠናዎች ለመናንያን ቢሰጣቸው ያሉትን ችግሮች ሙሉ በሙሉ መፍታት ባይቻልም የመናንያንን ፍልሰት በትንሹ መቅረፍ ይቻላል። በተጨማሪም አዲስ ለሚመጡ መናንያን ከነባሩ ጋር መጓዝ ለማይችል አንድ ጊዜ ቀኖና ከመጫን ደረጃ በደረጃ እንደ ቆይታው መጠን እንዲለማመደው ቢደረግ እንዲሁም ተተኪ መናንያን ለማፍራት ሁሉም ገዳማት እና መናንን ዐቅደው መሥራት እንዳለባቸው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና መስጠት።
ገዳሙ ላይ ያለው ተግዳሮት
ገዳማዊ ሕይወት በራሱ ከፈተና ያልተለየ ሕይወት ቢሆንም ከላይ ካየናቸው ሰፋፊ የልማት ሥራዎች አንጻር የገዳሙ ዋና ፈተና የመናንያን ፍልሰት ነው። ወደ ገዳሙ ለሚመጡ መናንያን ልዩ አቀባበል ቢደረግላቸውም በገዳሙ ውስጥ ከሚከናወኑ በርካታ ተግባራት እና የጉልበት ሥራዎችን
በመሰላቸት አብዛኛዎቹ መናንያን ለመቆየት ፈቃደኛ አይደሉም።
ገዳሙ ላይ ያለው ተግዳሮት
ገዳማዊ ሕይወት በራሱ ከፈተና ያልተለየ ሕይወት ቢሆንም ከላይ ካየናቸው ሰፋፊ የልማት ሥራዎች አንጻር የገዳሙ ዋና ፈተና የመናንያን ፍልሰት ነው። ወደ ገዳሙ ለሚመጡ መናንያን ልዩ አቀባበል ቢደረግላቸውም በገዳሙ ውስጥ ከሚከናወኑ በርካታ ተግባራት እና የጉልበት ሥራዎችን
በመሰላቸት አብዛኛዎቹ መናንያን ለመቆየት ፈቃደኛ አይደሉም።
መፍትሔ ሊሆኑ የሚችሉ
ለመናንያን ፍልሰት መፍትሔ ሊሆን የሚችለው በዋናነት አጽንኦ በዓት ሲሆን ይህም የሚሆነው አግዚአብሔር ሲፈቅድ እና ሲያጸና መሆኑ በእርግጥ ይታወቃል። ይሁን እንጂ እንደ ሰው ሰውኛ መናንያን በበዓታቸው እንዲጸኑ የተለያዩ ሥልጠናዎች መሥጠትም አንድ መፍትሔ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ የምንኵስና ሕይወት ያሉት ፈተናዎች እና የሚየሰጠው ጸጋ አጽንኦ በዓት እና ሌሎች ተዛማች ሥልጠናዎች ለመናንያን ቢሰጣቸው ያሉትን ችግሮች ሙሉ በሙሉ መፍታት ባይቻልም የመናንያንን ፍልሰት በትንሹ መቅረፍ ይቻላል። በተጨማሪም አዲስ ለሚመጡ መናንያን ከነባሩ ጋር መጓዝ ለማይችል አንድ ጊዜ ቀኖና ከመጫን ደረጃ በደረጃ እንደ ቆይታው መጠን እንዲለማመደው ቢደረግ እንዲሁም ተተኪ መናንያን ለማፍራት ሁሉም ገዳማት እና መናንን ዐቅደው መሥራት እንዳለባቸው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና መስጠት።
ማጠቃለያ
በአጠቃላይ በምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት በዱግዳ ቦራ ወረዳ የሚገኘውን የመካነ ሕይወት ጮቢ በዓታ ለማርያም አንድነት ገዳምን ከሚገኝበት ቦታ በመነሣት መቼ እንደተመሠረተ ከተመሠረተበት ጀምሮ ያከናወናቸውን ተግባራትና የገዳሙን ታሪክ በአሁኑ ሰዓት ገዳሙ ያለበትን ነባራዊ ሁኔታ ከረጅሙ በዐጭሩ አቅርበናል። እግዚአብሔር አምላክ ከገዳሙ በረከት ያድለን አሜን
