የገዳሙ መገኛ ቦታ፡- መካነ ሕይወት ጮቢ በዓታ ለማርያም አንድነት ገዳም የሚገኘው በምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት በዱግዳ ቦራ ወረዳ ሀርቦ አቡኖ ቁሙሮ ቀበሌ ገበሬ ማኅበር ነው፡፡ በመካከለኛው ምሥራቅ አቅጣጫ ከአዲስ አበባ እስከ ኬላ ከተማ ድረስ ፻፲፫ ኪሎ ሜትር ርቀት ያለው ሲሆን፤ ከኬላ ከተማ ገዳሙ ድረስ ደግሞ ያለው ጥርጊያ መንገድ ፲፭ ኪሎ ሜትር ይሆናል፡፡ "ጮቢ" ማለት በኦሮሚኛ በረከት ማለት ሲሆን፤ የገዳሙ አካባቢ ደግሞ አቡኖ በመባል የሚጠራ ነው፡፡ ይህንንም ስያሜ ያገኘበት ምክንያት በጥንት ጊዜ ቦታው ላይ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ እና አቡነ ተክለ ሃይማኖት ያረፉበት በመሆኑ እንደሆነ የገዳሙ አባቶች ያስረዳሉ፡፡ ከገዳሙ በስተ ምዕራብ አቅጣጫ በተራራ የተከበበ እና የተለያዩ ዕፅዋቶች የሚገኙበት ሲሆን፣ ሰፋፊ የእርሻ መሬት ያለበት ሜዳ እና ገደላማ ነው፡፡ በገዳሙ አካባቢ የሚኖሩ ምዕመናን የሶዶ ጉራጌ ሲሆኑ፤ መለያ ስማቸው ግን ሶዶ ክስታኔ በመባል ይታወቃሉ፡፡ ይህንንም ስያሜ ያገኙት በጣሊያን ጊዜ በመስቃን ጦርነት ከአርሲ ሙስሊሞች ጋር ተዋግተው ብዙዎች ሰማዕትነት ተቀብለዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በግራኝ አሕመድ ወረራ ጊዜም ሃይማኖታቸውን ሳይቀይሩ ፀንተው የቆዩ ክርስቲያኖች በመሆናቸው ነው፡፡
መካነ ሕይወት ጮቢ በዓታ ለማርያም አንድነት ገዳም የተመሠረተው በእግዚአብሔር መልካም ፈቃድ በ፲፱፻፺፫ ዓ.ም. ነው፡፡ መሥራቹም የምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል የሆኑት ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ሣልሳዊ ናቸው፡፡ አሁን እየተጠራበት ያለውን ስያሜ ያገኘው ግን ሰኔ ፬/፲፱፻፺፰ ዓ.ም ነው፡፡ ዛሬ የሚታየው ልማት ከመምጣቱና ከመስፋፋቱ በፊት ቦታው ጠፍ እና ምንም የሌለበት የእርሻ መሬት ነበር፡፡ በወቅቱ ፭ እናቶች እና ሁለት አባቶች በጊዜው ቡታጅራ ማረሚያ ቤት ለእስር ከተዳረጉ እና የእስር ጊዜቸውን ጨርሰው በነጻ ከተለቀቁ በኋላ ወደ ሥፍራው በማቅናት አከባቢውን ሲቃኙ አስቀድሞ ቦታው ለእግዚአብሔር ማደሪያ የተመረጠ መሆኑን በመረዳት በእኒሁ አባቶች እና እናቶች ተነሣሽነት በብፁእ አቡነ ጎርጎርዮስ ሣልስ የምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ መልካም ፈቃድ የመሠረት ድንጋይ ተቀመጠ፡፡ ለሐሳቡ እውን መሆን አቶ አማረ ዱቤ የሚባሉ የአከባቢው ነዋሪ እና የሀገር ሽማግሌ የሆኑ የአባቶችን ሐሳብ በመቀበል የራሳቸውን የእርሻ መሬት ለቤተ ክርስቲያኑ በመስጠት አሁን ያለችው የቤተ ክርስቲያን መቃኞ ሰኔ ፲፭/ ፲፱፻፺፭ ዓ.ም. ተጀምሮ በ፮ ወር ታንጾ ታኅሣሥ ፫ ቀን ፲፱፻፺፮ ዓ.ም. ተጠናቆ ቅዳሴ ቤቷ ተከበረ፡፡
በተለይ አሁን ያሉት የገዳሙ አበ ምኔት መ/ር አባ ተ/ሥላሴ በሳል የአመራር ሰጪነት በአባ ገ/እግዚአብሔር እና አባ ኃ/ገብርኤል አጋዥነት የመጀመሪያ ተግባር የነበረው የገዳሙን ይዞታ ማስፋፋት ስለነበር እስከ ፲፱፻፺፰ ዓ.ም. ይህን ዐቢይ ተግባር በሰፊው ቀጥለውበታል፡፡ የገዳሙ ይዞታ ፹፩.፸፱ (ሰማንያ አንድ ነጥብ ሰባ ዘጠኝ) ሄክታር ሲሆን የይዞታ ማረጋገጫ ደብተርም ተሰጥቶታል፡፡ ወደ ፊትም ይዞታን የማስፋቱ ሥራ የሚቀጥል ይሆናል፡፡ የእኒህ አባቶች ምኞት እና ራእይ ለትውልዱ አርዓያ የሚሆንና ለችግረኞች መጠጊያ ሊሆን የሚችል ገዳም መመሥረት በመሆኑ ከሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ጎን ለጎን ተግባር ቤት እና የእናቶች ማደሪያ ሠሩ፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ገዳሙ፣ የገዳሙ መናንያንና ልማት የማይነጣጠሉ የአንድ ሳንቲም ገጽታ ሆኑ፡፡